#KALTUBE

ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተሞልቶ በእኛ አደረ። ዩሐ1÷ 14
” Daily Spiritual Feeding”
በዚህ ያገኙናል👉 @Kaltube_bot

የዩቲዩብ ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ👇
https://youtube.com/c/KALTUBEOfficial

ዘጠነኛ ቃልኛ ዲጂታል መፅሔታችን👇
https://t.me/KALTUBE/9618

Recent Posts

" አካል ተግባር እንጂ ሀሳብ የለውም" በወንድም ሰይፉ ዘሪሁን

https://youtu.be/6VS5Wa-Vxm0?si=gmJxqYuiPGcUNH64
"ንጉሣችን ሆይ "

ንጉሥ ስሙ እራሱ የሚያስፈራ ሲጠራ አፍ እንደሚሞላ ልብንም የሚያሞቅ ሞገስ ያለው፣ እንደ ስሙ የሆነ ፣ ባማረ ዙፋን ላይ የሚቀመጥና በክብር የተሽሞነሞነ ነዉ። ህዝቡ አቅጣጫ የለሽ እንዳይሆን ከፊት መሪ ፣ፍትህን የሚያሰፍን፣ አጥፊውን የሚቀጣ ባለስልጣን ነው ንጉሥ። ህዝብ መሪውን ይመስላል። ዋልጌ ንጉሥ ህዝቡን ዋልጌ ያደርጋል፤ ጣኦት አምላኪው ህዝቡን ጣኦት ያስመልካል፤ አመንዝራው ህዝቡን ያሴስናል፤ ጠማማው ህዝቡን ያጠፋል፤አምላኩን የሚፈራው ደግሞ ህዝቡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ያደርገዋል።


ታዲያ አንድ ንጉሥ አለ ንግሥናው የአለም ፍልስፍናና ጥበብን መሳለቂያ ያደረገ። የእርሱ ሹመት መጀመሪያ የለውም፤ አገዛዙም የጊዜ ገደብ አልተበጀለትም መዝሙር 45፥6። ሰለሞን በንግሥናው ዘመን ዙፋኑን ከዝሆን ጥርስ በከበረ ወርቅ ለብጦ ሰራ 1ነገ 10:18 ። እርሱ ከሰለሞን የሚበልጠው የዘለአለም ንጉስ ግን ዙፋኑን መስቀል አደረገ። የአባቱ ፈቃድ ነበረና የመስቀል ላይ ህመምን ክብር ብሎ ጠራው። የንጉሥ ግርማና ክብር አልነበረውም ነገር ግን ታይቶ የማይወደድ መልክን ያዘ። ውበቱን በፈሰሰው ደሙ፣ ደም ግባቱንም በጣሩ ውስጥ አደረገ።


ንግስናው በንቀት የታጀበ ነበረ። ይሄ ንጉሥ እንደ ሌሎቹ ነገስታት ያጠፋውን ሊቀጣ አልመጣም፤ ይልቁንም የአጥፊውን ቅጣት ተቀበለ ፤ፈራጅ ሳይሆን ፍርደኛ። በእንጨት ሰቅለው ከምድር ከፍ ባደረጉት ጊዜ ሀጥያተኛውን ወደ ሰማይ ያስጠጋ የህማም ሰው ነው። የመንግስቱን ደጅ ሰማይን ከምድር ባስታረቀ በደሙ በከፈተ ጊዜ ታዳሚዎቹን ስማቸውና ግብራቸው በራሱ ስምና ግብር የተካላቸውን የቀድሞ ህመምተኞች ፣አመፀኞች ፣ሀጥያተኞች ፣ነውረኞች ፣በደለኞች ፣ውዳቂና ሞኞችን አደረገ።


እርሱ የሥላሴን ፍቅር የገለጠ መለኮት ፣የእግዚአብሔር ልጅ ፣እራሱም እግዚአብሔር ነው። አምላክነቱ ሰው ከመሆን ያልከለከለው ትሁት ጌታ። በዝቅታው የከፍታን ጥግ፣ በውርደቱም የክብርና የሉአላዊነትን ጫፍ ወርሷልና የሰማይ የዘለአለም ዜና ነው።


ንጉሣችን ሆይ መንገዱ ለጠፋብን መንገድ ፣ለጨለማችን ብርሀን ሆንክልን። በፅድቅህ ጻድቃን፣ በመልክህ ውቦች አርገህ ለአባትህ መንግስት ብቁ አደረግከን። በህመምህ ተፈውሰን በጩኸትህ ተሰማን፤ በእንባህ ውስጥ አብ አይቶን በጣርህ ድነናልና መድሀኒትና ንጉሣችን ሆይ የዘለአለም መዝሙራችን ነህ።


ራእይ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁴-⁵ ... ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥
⁶ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።


       @KALTUBE
🖥የልመናዬን ድምፅ

🗣️“እግዚአብሔር የልመናዬን ድምፅ ሰምቶአልና ወደድሁት።”

— መዝሙር 116፥1


ሕይወት ሁልጊዜ በለምለሙ መስክ ማረፊያዊያን አታደርግም። ምንም እንኳን ዘመኗን በዚህ ስፍራ መጨረስ ብትፈልግም እውነታው ግን ይህ አይደለም። ደረቅ በሆነ ምድረ በዳ ራሷን የምታገኝባቸው አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ። ዳዊት ከባድ የሆነ የህይወት ማዕበል ውስጥ ገብቶ እንደ ነበር ይናገራል። “የሞት ጣር ያዘኝ፥ የሲኦልም ሕማም አገኘኝ፤ ጭንቀትንና መከራን አገኘሁ።” (መዝ 116፥3) በእርሱና በሞት መካከል አንድ እርምጃ እስኪቀር ድረስ የሞት አፋፍ ላይ ደረሰ።


ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆን ዳዊት ራሱን በጭንቀትና በመከራ አስሮ ከማስቀመጥ ይልቅ ፊቱን ለነገሮች ሁሉ መፍትሄ ወደ ሆነው አምላክ በማቅረብ “ነፍሴን አድናት” (ቁ 4) በማለት ቃተተ። እግዚአብሔር አምላክ ቸር በመሆኑ ዳዊትን ከሞት ታደገው፤ እረፍትንም ሰጠው። ዳዊት፣ ከሲኦል ጣር መውጣት ከሆነለትና የሞት አዋጁ ከተሻረለት በኃላ ይህን ሁሉ ላደረገለት አምላክ ምስጋናውን አቀረበ። “እግዚአብሔር የልመናዬን ድምፅ ሰምቶአልና ወደድሁት። ጆሮውን ወደ እኔ አዘንብሎአልና በዘመኔ ሁሉ እጠራዋለሁ።” (ቀ 1-2)


እኛስ ስንት ጊዜ ይሆን ከሞት ጣር የዳንን? ስንት ጊዜስ ይሆን በሀዘንና በጭንቀት ነፍሳችን ዝላ ሳለ ዕረፍትን ያገኘን? አባጣ ጎርባጣ የነበረው የሕይወት ጎዳናችን በአምላካችን እርዳታ ቀና መንገድ ሆኖልናል። ትላንት አልቅሰን፣ ዛሬ ላይ ስቀናል። ባለፈው ዘመን ተሰብረን፣ አሁን ላይ ግን መጠገን ሆኖልናል። ይህ ከእኛ የሆነ ነገር አይደለም። ሁሉም የሆነው ከእግዚአብሔር ነው። አዎ፣ እግዚአብሔር የልመናን ድምፅ የሚሰማ፣ ጭንቀትን የሚያደምጥና መልስ የሚሆን መልካም አምላክ ነው።


🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ በጨነቀኝ ጊዜ ደርሰህ ከሞት ጣር ስላዳንከኝ አከብርሃለሁ። አቤቱ፣ ዛሬም ተመስገን እልሃለሁ። አሜን።
💬  የህይወት ስንቅ ~ #BT
 🔗🔗@KALTUBE
በክርስቶስ   IN CHRIST
ክፍል 56

       ህይወት መንፈሳዊ ነው

የሰው ልጅ ህይወት ከማይታየው ዓለም ጋር (ከእግዚአብሔር ዓለም ጋር አሊያም ከሰይጣን ዓለም)ጋር ቀጥተኛ ወይም ተዘዋዋሪ ግንኙነት አለው።

➢በተለይ በአፍሪካ አህጉር አንድ ህፃን ልጅ ገና በእናቱ ማዕፀን ሳለ በወላጆቹ ሙሉ ፈቃድ  ለአጋንንቱ ዓለም ታልፎ ይሰጣል። ታልፎ ከተሰጠበት ደቂቃ አንስቶ አጋንንቶች ለአዓላማቸው መሳካት ለህፃኑ ልዩ እንክብካቤ ያደርጉለታል። ሲወለድ በጨለማው ዓለም ስም ይወጣለታል፣የወደፊቱ እጣ ፈንታዉ ይወሰናል፣ኃይል የተሞሉ ሰይጣናዊ ትንቢቶች ይደገሙበታል። ከዛ ይህ ህጻን አድጎ እንደ ማንኛውም ሰው ትምህርት ቤት ይገባል ከዛ አቋርጦ ተንከራታች ይሆናል፣ስራ ይጀምራል ስኬት ግን አይኖረውም ፣ያገባል ትዳሩ የተቃወሰ ይሆናል፣ያቅዳል እቅዱ ይጨነግፋል። ታሞ እንኳ ህመሙን ዶክተር መለየት እስኪያቅተው ድረስ መከራ ያያል።

➢ይህ ሰው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አምኖ  ነፃ እስኪወጣ ድረስ በማያቀውና በማይጨበጥ ገመድ ታስሮ  በእንቆቅልሽ የህይወትን ተራራ እየገፋ ይኖራል። ህይወት መንፈሳዊ እንደሆነ የማይረዱ ሰዎች ሁሉም ነገር በድንገት የሚከሰት ይመስላቸዋል። ሁሉንም  ነገር ያለ መንፈሳዊ እገዛ በቁጥጥራቸው ስር ማዋል እንደሚችሉ ያስባሉ፣አጋንንት ያደረበትን ሰው በህክምና ሳይንስ ለመፈወስ ይጥራሉ፣ መንፈሳዊ ነገር ቅዠት እንደሆነ ያስባሉ፣  አጋንንት ያደረበትን ሰው በኢየሱስ ስም ነጻ ከማውጣት ይልቅ የስነልቦና ምክርና ልዩ እንክብካቤ በማድረግ እንዲሻለው ይጥራሉ።

       የሚታየው ከማይታየው ነው

የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን። ይላል። ዕብ 11:3

ሐዋርያው
  ቅዱስ ጳውሎስ በእምነት ስለመኖርና  በእምነት ነገሮችን  በጥልቀት ስለማየት ሲያስረዳን የሚታየውን ፍጥረት ምሳሌ በማድረግ ቀድሞ ከመታየቱ በፊት በመንፈስ ዓለም የነበረ መሆኑ ያስረዳል። የሚታየው ተዘጋጅቶ የተገለጠው ከማይታየው ዓለም ነው። አንድ ነገር አላየነውም ማለት የለም ማለት አይደለም። እምነት ስጋዊ አይኖች የማያዩትን ማየት፣ስጋዊ ጆሮ የማይሰማውን መስማት ያስችላል።
➢ከነገሮች በስተጀርባ መንፈስ ዓለም አለ።
እያንዳንዱ ሰው ወይ በጌታ ነው ወይም በሰይጣን ነው። መሀከል ላይ( Neutral) መሆን አይቻልም። ምክንያቱም ህይወት መንፈሳዊ ነው።ከመንፈሳዊ ዓለም ተፅዕኖ ማምለጥ አይቻልም።

➢ አባቶቻችን ይህን የመንፈስ ዓለም ስርዐት ስለተረዱ ለነሱ ህይወት ልዩ ትርጉም ነበረው። ህይወት መንፈሳዊ መሆኑን ስለተረዱ ይፀለዩ ነበር፣ይፆሙ ነበር፣ህብረት ያደርጉ ነበር፣ መንፈሳዊ ውጊያዎችን በእምነት ፀንተው ይዋጉ ነበር፣በረከት የልፋት ውጤት አለመሆኑን ስለተረዱ እጃቸውን ወደ ሰማይ ይዘረጉ ነበር፣ የማይቻል ነገር ሲገጥማቸው ለተዓምራት እጃቸውን ወደ ሰማይ ይዘረጉ ነበር፣ ሞገስ ለማግኘት ሲፈልጉ እግዚአብሔርን በመፍራት ይመላለሱ ነበር።ለውጊያ ሲወጡ የእግዚአብሔርን አብሮነት ይጠይቁ ነበር።
ምክንያቱ የስኬት የድል ምስጢር ከመንፈሳዊ ዓለም እንደሚመጣ ተረድተዋልና።

➢መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስናጠና የነገውን መጪ ሁኔታ ለማወቅና የእግዚአብሔርን ስትራቴጂካዊ አጀንዳ ለመረዳት ሲሉ ወደ ነቢያት ይመጡ ነበር።በተቃራኒው ደግሞ
ከጥንቆላ እና ከጨለማው የመናፍስት ዓለም ጋር ቁርኝት የነበራቸውን ነገስታት፣ነጋዴዎች፣ ባለጠጎች ታሪክ እናነባለን።(ሐዋ 13:8፤ ዳን 2:1-3)። ምክንያቱም የሰው ነፍስ አጋዥ ኃይል
ትፈልጋለች። የሰው ነፍስ ክፍተቷን ለመሙላት
ወደ መንፈሳዊው ዓለም ትጠጋለች። መጥፎነቱ ሰይጣን የነፍስን ክፍተትና ባዶነት ማባባሱ።

➢እንደ አማኝ የእግዚአብሔር ዓለም ስርዓትን ለመረዳት 4 ነገሮች አስፈላጊ ናቸው።
  1-እምነት
  2-መንፈሳዊ መርሆችን መከተል
  3- መገለጥ
  4- የእግዚአብሔር ቃል
እነዚህን አራት መንፈሳዊ ትጥቆች መታጠቅ እግዚአብሔር በልጁ በክርስቶስ አስቀድሞ የደረሰውን ህይወት እንድንተውን አቅም ይሆነናል።
➢እንደ አማኝ ለመንፈሳዊ ህይወት ያለን ንቃተ ህሊና ሊጨምር ይገባል። ለመንፈሳዊ ህይወት ንቁ(Active) ስንሆን የመንፈሳዊ ዓለም ስርዓት ውስጥ በቀላሉ መመላለስ እንችላለን።
መንፈሳዊ ንቃተ ህሊና የሚመጣው ደጋግሞ የእግዚአብሔርን ቃል በማንበብና በማሰላሰል እንዲሁም ለመንፈሳዊ ህይወት ግብዓት የሆኑ ነገሮችን ሁሉ በመሰብሰብ ነው።

መንፈሳዊነታችን የሚለካው ለመንፈሳዊው ባለን ንቃተ ህሊና ልክ ነው።  አስተሳሰባችን ለመንፈሳዊው ምን ያክል ንቁ ነው ?

መሳይ አለማየሁ(ነቢይ)

ክፍል 57 ይቀጥላል

👇💐👇💐👇💐👇💐👇💐
            @KALTUBE
            @KALTUBE
            @KALTUBE
የዕብራውያን መጽሐፍ ተከታታይ ትምህርት | በሰይፍ ዘሪሁን

https://youtube.com/live/36cQ7ENwOGc
በክርስቶስ  IN CHRIST
ክፍል 55

         የትኩረት ኃይል

  በራሳችሁ  ጉዳይ ላይ ብቻ አተኩሩ
(1ተሰ4:11) አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ትኩረት (FOCUS ) ማለት አዕምሮን፣ ጉልበትን፣ጊዜን፣ገንዘብን ሁሉ በአንድ ልታሳኩ በምትፈልጉት ነገር ላይ በአግባቡ የማዋል ብቃት ነው። ትኩረት በህይወት ጉዳዮች ላይ ኢላማ ማድረግም ነው። ትኩረት መፈፀም ላሰብነው ጉዳይ ላይ በደንብ ማሰብና እስከሚፈፀም ድረስ ማሰብ አለማቆምም ነው  ።

➢ ትኩረት ያልተደረገበት የትኛውም የህይወት ጉዳይ ውጤታማ አያደርግም።ትኩረት ለህይወት እጅግ እጅግ ጠቃሚ ነው።
አዕምሯችን በየማይክሮ ሰከንዱ የተለያዩ አይነት ሃሳቦችን ያመነጫል። ወደ ተግባር የሚቀየረው ግን ትኩረት የተሰጠው ሃሳብ ብቻ ነው።
➢አዕምሮ ስላሰበ ብቻ ያሰብነው ሁሉ ትኩረት አግኝቷል ማለት አይደለም። ስለዚህ ሊተገበሩ የተፈለጉት ሃሳቦች ላይ የበለጠ ማሰላሰልና በጥልቀት መመልከት የትኩረት መገለጫዎች ናቸው።

ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ዋና ዋና የህይወት ጉዳዮች

1ኛ ዓላማችሁ(ራዕያችሁ) ላይ ትኩረት አድርጉ

ዓላማችሁ(ራዕያችሁ) ላይ ትኩረት ማድረግ ሲባል ከጅማሬ እስከ ፍፃሜ ድረስ ያሰባችሁትን እስከምታሳኩ ድረስ ትኩረት ማድረግ ነው።
አንድን ነገር አሳካለሁ ብላችሁ ካሰባችሁ ትኩረት ማድረግ አለባችሁ። ትኩረት ካልሰጣችሁት የትኛውም ሃሳብ ሃሳብ ብቻ ሆኖ ይቀራል።ወደ ተግባር ሊቀየርና ፍሬ ሊያፈራ አይችልም።
ምሳሌ:-
እስቲ አስቡት ሁለት ሊጋቡ ያቀዱ ባልና ሚስት ስንት ጊዜ ይሆን ስለ ትዳር መያዝ የሚያስቡት?ምን ያህል ጊዜ እንሚያወሩበት፣እንደሚወያዩበት አስቡት??? ይህ ብቻ አይደለም ትዳራቸው እንዲመሰረት የማያደርጉት ቅድመ ዝግጅት የለም።ገንዘባቸውን፣ጊዜያቸውን፣ግንኙነታቸውን፣ ጉልበታቸውን ሁሉ ለጋብቻቸው ቀንና ለትዳራቸው ህይወት ያፈሳሉ።
እነዚህ ጥንዶች ስለ ትዳር አንድ ቀን ብቻ አስበው ወደ ትዳር አይመጡም። ደጋግሞ ማሰብ ፣ማሰብ ፣ማቀድ፣ማቀድ፣ያስፈልጋቸዋል።ያላቸውን ሁሉ ላሰቡት ነገር መሳካት ሊያውሉት ይገባል።
ትኩረት የተደረገበት ነገር ውበት አለው።ልታሳኩ ያሰባችሁት በትኩረት እጦት እንዳይሞት ትኩረት አድርጉ።
አንድ ነገር ለማሳካት ተነስታችሁ መንገድ ላይ ሀያ ሁለት ነገር ሲገጥማችሁ በነሱ አትወሰዱ።የጀመራችሁትን ለማሳካት የሙጥኝ በሉ።

2ኛ ቤተሰባዊ ህይወታችሁ ላይ ትኩረት አድርጉ

ሌላው ዋነኛው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ቤተሰባዊ ህይወት ነው።ይህም አጠቃላይ የቤተሰብ ህይወትን ይመለከታል።ይህም ትዳርን፣የልጆች አስተዳደግን ወዘተ ሁሉ ያጠቃልላል።
ቤተሰብ የማህበረሰብ፣የሐገር ሁሉ መሰረት እንደሆነ ይታመናል። ስለሆነም ልዩ ትኩረት ይፈልጋል። ጤናማ ቤተሰባዊ ህይወት የጤናማ ማህበረሰብና ሐገር ምስጢር ነው።ትኩረት ያልተሰጠው ቤተሰብ በእንቆቅልሽ የተሞላ፣ፍፃሜውም በፍቺ የሚጠናቀቅ ሊሆን ይችላል። ትኩረት ያልተሰጠው ቤተሰብ መፅናት አይችልም።

3መንፈሳዊ ህይወታችሁ ላይ ትኩረት አድርጉ

ሌላው ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ጉዳይ የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር ያለው መንፈሳዊ ህብረት ነው።

ትኩረት ስታደርጉ ብዙ ነገር ሊያባክናችሁ አይችልም።እናንተም አቅማችሁን ሰበስባችሁ በዒላማ መኖር ያስችላችኋል።
ትኩረት ያላችሁን አቅምና ሃብት ሁሉ በማይሆን ነገር ላይ ፈሰስ እንዳታደርጉ ይቆጥባችኋል።

         ትኩረት ስታደርጉ
-አቅማችሁን ከማባከን ትድናላችሁ፣
-የጊዜ አጠቃቀማችሁ ይስተካከላል፣
-አላማችሁን በተፈለገው ጊዜ ውስጥ ማሳካት ትችላላችሁ፣
-ካላስፈላጊ ግንኙነቶች ትቆጠባላችሁ፣
-ገንዘባችሁን በትርፋማ ነገር ላይ ማዋል ያስችላችኋል፣
-እውቀታችሁን ወደ ተግባር እንድትቀይሩ ያስችላችኋል፣
-ከወሬ፣ከስራ ፈትነት ህይወት ተቆጥባችሁ እንድትኖሩ ያስችላችኋል፣
- ጤናማ መንፈሳዊ ህይወት ይኖራችኋል

በመጨረሻም  ትኩረት ማድረግ የሌለባችሁ ነገር ላይ ትኩረት አታድርጉ። እጅግ ብዙ ሰዎች ትኩረት የሚያደርጉት ትኩረት ማድረግ በሌለባቸው ተራ ነገር ላይ ነው።ለምሳሌ ;-
የሰዎች አሉባልታ ላይ፣ወሬዎች ላይ፣ ትኩረት በማድረግ ያላቸውን ነገር ሁሉ የሚያባክኑ ጥቂት አይደሉም።ፍሬ ቢስ በሆነ ነገር ላይ የትኛውንም ያክል ትኩረት ቢደረግ ለውጥ የለውም።በማይሆን ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ የውስጥ ብቃትንና ሃይልን ሁሉ የመግደል ጉልበት አለው።

ዛሬ ንቁና ትኩረታችሁን በአስፈላጊና ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮቻችሁ ላይ አድርጉ።

መሳይ አለማየሁ (ነቢይ)

ክፍል 56 ይቀጥላል

👇💐👇💐👇💐👇💐👇💐
            @KALTUBE
            @KALTUBE
            @KALTUBE
በክርስቶስ    IN CHRIST
ክፍል 54

    የዲያብሎስን ሽንገላ መርታት

ዲያብሎስ በማታለል የረጅም ጊዜ ልምድና ጥበብ ያለው የወደቀ መልአክ ነው።  ዲያብሎስ ሰዎችን በመሸንገል ቢያንስ 5 ሺህ አመታት አስቆጥሯል።

የዲያብሎስ ሽንገላ በአብዛኛው በየዘመናቱ ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን በተመሳሳይ ሽንገላው ደግሞ የብዙዎችን ፍፃሜ አበላሽቷል።በዲያብሎስ ሽንገላ አልታለልም ብለው የነቁ፣ የወሰኑና የእግዚአብሔር ፀጋ የረዳቸው አባቶቻችን ግን ነቅተው በመቃወም ለዲያብሎስ ጠንቅ ሆነው ኖረው አልፈዋል።

➢ቃሉ እንደሚያስተምረን ፣ዲያብሎስ ሰዎችን በሶስት ዋና ዋና አቅጣጫዎች ይሸነግላል፣

1ኛ ጤናማ  አመለካከት በማዛባት ይሸነግላል

ሰዎች ትናንት የነበራቸውን በእግዚአብሔር ፍርሀት የተሞላ አስተሳሰቦችን እየጣሉ ወደተበላሸ አስተሳሰብ ውስጥ እንዲገቡና ቀዩን የህይወት መስመር ጥሰው እንዲሄዱ አሳማኝ ምክንያት ያቀርባል። ሰይጣን የብዙዎችን አመለካከት የሚበርዘው በትምህርትና በእውቀት ነው። ለዛ ነው በመጨረሻው ዘመን ሰዎች የአጋንንትን ትምህርት ወደመስማት ጆሯቸውን ያዘነብላሉ የሚለው ቃሉ።

➢ትምህርት አመለካከትን በቀጥታ የመቀየር ኃይል ስላለው ሰይጣን የሐሰት ትምህርቶችን ተጠቅሞ የብዙዎችን አቋም ይሸረሽራል።

ምናልባት ትናንት ጤናማ አስተምህሮ ይከተል የነበረው ወንድም ዛሬ ልዩ ትምህርትና አስተምህሮ ሲያራምድ ልናይ እንችላለን። ይህ ወንድም አመለካከቱን ሲቀይር ለሱ አዲስ መገለጥ ውስጥ የገባ ይመስለው ይሆናል። ነገር ግን አይደለም።

መገለጥ የትናንቱን መሰረት የሚንድ ሳይሆን የሚያጠናክር መንፈሳዊ መረዳት ነው። መገለጥ መሰረታችንን ያፀናል እንጂ መሰረታችንን አያናጋም።

የአመለካከታችን ጤናማነት ሁሌም የሚለካው በእግዚአብሔር ቃል ነው።

መቼም ቢሆን በእግዚአብሔር ቃል ላይ አናድግም። የእግዚአብሔር ቃል መመርያችን መመዘኛችንና  ፈራጃችን ነው።ስለዚህ ሽንገላውን ለማሸነፍ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይለናል።

አጥብቀህ ልብህን (YOUR MIND) ጠብቅ
የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና።(ምሳሌ 4:23 )ይላል።


2ኛ የእግዚአብሔርን ፀጋ አለአግባብ እንድንጠቀም ይሸነግላል

ጠላት የእግዚአብሔርን ፀጋ የኃጢአት ማበረታቻ አድርጎ የሰው አዕምሮ ላይ ከሳለ ሰው ፀጋውን እያመካኘ በሀጢአት ደጋግሞ ይወድቃል።ምክንያቱም ሰይጣን በሰው አዕምሮ ወሰጥ የማሳመን ስራ ሰርቷልና።

የእግዚአብሔር ፀጋ ግን የኃጢአት መዳኛና ማምለጫ እንጂ የኃጢአት ማበረታቻ አይደለም።

3ኛ እግዚአብሔርን መፍራት ትርጉም እንደሌለው ያስተምራል

ሰይጣን በዚህ መንፈስ የሸነገላቸው ሰዎች ሊበራል ሆነው ዘመናዊ-አለማዊ በመሆን ይኖራሉ። ሰዎች ሊበራል ሲሆኑ ጠያቂ አይፈልጉም።መገዛት አይፈልጉም። መመራት አይፈልጉም።ዲሲፕሊን አይወዱም። ራሳቸውን አይገዙም። ሁሉን እያደረጉ በምኞትና በፍትወት ይመላለሳሉ። በሰይጣን ስለተሸወዱ ህይወታቸውን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሳይሆን እንደፈለጉ እየመሩ ይመላለሳሉ።

ዲያብሎስ ይመጣና እንዲህ ይላል  እግዚአብሔርን መፍራት አጉል እና አክራሪ ክርስትና ነው ስለዚህ ህይወትን አታክርረው፣ ''አንተ ለየት ያልክ ፍጡር አይደለህም'' ፈታ በል፣ዘና በል፣ምን ችግር አለው ይልሀል።

ያኔ በዲያብሎስን ሽንገላ  የተታለለ ሰው ኃጢአትን ምን ችግር አለው ወደሚል መንፈስ ይገባል።

ስለዚህ የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። - ኤፌሶን 6:11

ቃሉን እናንሳ።
ትኩረት ለእግዚአብሔር ቃል እንስጥ!

መሳይ አለማየሁ (ነቢይ)

ክፍል 55 ይቀጥላል

👇💐👇💐👇💐👇💐👇💐
            @KALTUBE
            @KALTUBE
            @KALTUBE
 በክርስቶስ     IN CHRIST    
ክፍል 53
          
      በመንፈስ ሃይል ላይ መደገፍ

መልሶም። ለዘሩባቤል የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።ታላቅ ተራራ ሆይ፥ አንተ ምንድር ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ፤ ሰዎችም። ሞገስ፥ ሞገስ ይሁንለት ብለው እየጮኹ እርሱ መደምደሚያውን ድንጋይ ያወጣል ብሎ ተናገረኝ። (ትንቢተ ዘካርያስ 4 :6- 7)

➢በህይወታችን ከተፈጥራዊ አቅማችን በላይ የሆኑ ብዙ እልፍ ነገሮች አሉ።ሁሉም ነገር በሃይላችንና በብርታታችን የሚቻል አይደለም።
ህይወት በራሳችን ጥረት ብቻ የምናስቀጥላት አይደለችም።ከአቅማችን በላይ ያሉ ነገሮች ስላሉ የእግዚአብሔር መንፈስ እርዳታ ያስፈልገናል።

➢በህይወት መንገድ ውስጥ አለመቻል ሲመጣ የሚያስችል፣ድካም ሲመጣ የሚያበረታውን የጌታን መንፈስ በሙሉ ልባችን ልንደገፍ ይገባል።
ያለ እርሱ ምንም ትርጉም ያለው ነገር ማድረግ አይቻልም።

➢መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ሃያላን የእግዚአብሔር አገልጋዮችና ህዝቦችን ሰው አድርጎ በነሱ ታላላቅ ስራ የሰራው መንፈስቅዱስ ነው።
 
➢ብዙ ጊዜ ሰው የመጨረሻውን አቅሙን አሟጦ ከጨረሰ በኋላ የእግዚአብሔር መንፈስ የሃይል ስራውን ይጀምራል።ምክንያቱም ለሰው የማይቻል ለእግዚአብሔር ይቻላልና።ለሰው የማይቻለውን ለመቻል መጣጣር ልፋት ብቻ ነው።
ለ12 አመታት ደም ይፈሳት የነበረችው ሴት ለ12አመታት ወደ ተለያዩ የህክምና ተቋማት(ባለመድሀኒት) ሄዳለች።ወደ ክርስቶስ እስከምትመጣ ድረስ ገንዘቧን ፈጀች ባሰባት እንጂ አልተፈወሰችም ይላል ቃሉ።ፈውሷ በገንዘብ ሃይልና በሰው ብርታት መገኘት አልቻለም።

➢የኤርትራ ባህር ከፊት የፈርዖን ሰራዊት ከኋላ ሲከብህ  የድሉ ምስጢር መንፈስ ነው።
የእግዚአብሔር መንፈስ በህይወታችሁ ሊሰራ የሚፈልጋቸው ትላላቅ ስራዎች ሲኖሩ መጀመርያ በራሳችሁ ምንም ማድረግ እንደማትችሉ በቃልም በተግባርም ያሳያችኋል።ከዛ መንፈሱን መደገፍ ስተጀምሩ ያኔ መንፈስቅዱስ ልዕለ ተፈጥሯዊ አሰራሩን ሲሰራ ትመለከቱታላችሁ።

➢ያለመንፈስ ቅዱስ ሃይል መኖርና መመላለስ ህይወትን አሰልቺና ተስፋ አስቆራጭ ያደርጋል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከውልደቱ እስከ ዕርገቱ ድረስ እያንዳንዷን ነገር ያደረገውና የሆነው በመንፈስ ነበር።
በመንፈስ ተወለደ፣በመንፈስ ተጠመቀ፣በመንፈስ ጠነከረ፣በመንፈስ ተቀባ፣ በመንፈስ ተአምራት ያደርግ ነበር፣በመንፈስ ከሙታን ተነሳ ከዛ በመንፈስ ወደ ሰማይ አረገ።

➢ስለዚህ የእግዚአብሔርን ፈቃድና ሃሳብ ኖሮ ለማለፍ፣ ለስኬትና ለድል የሚሆነው ምስጢር መንፈስቅዱስ እንደሆነ በጥልቀት ልንረዳ ያስፈልጋል።ጌታ ኢየሱስ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አይቻላችሁም ያለውን ቃል እናስብ።
እውቀታችን ከሚፈታው ችግር በላይ የማይፈታው ችግር ይበዛል።
ጥበባችን ከሚያደርገው ነገር በላይ የማያደርገው ነገር ይበልጣል።
ምርምራችን ከሚያገኘው በላይ የማያገኘው እውነታ ይበልጣል።
ስንቶቻችን እንሆን በመንፈስ  ሃይል ተደግፈን ለነገሮች መንፈሳዊ ምላሽ የምንሰጠው?        
የእግዚአብሔር ፀጋ ከሁላችን ጋር ይሁን።

ክፍል 54 ይቀጥላል

መሳይ አለማየሁ (ነቢይ)

👇💐👇💐👇💐👇💐👇💐
            @KALTUBE
            @KALTUBE
            @KALTUBE
በክርስቶስ IN CHRIST

ክፍል 52

        የሚኮንን ማነው?

ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርሱዋን አቁመው፦ “መምህር ሆይ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች። ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ?” አሉት።የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ፦ “ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት፡” አላቸው።
ዮሐ 8:3-7


➢ከላይ ያነበብነው ክፍል ጌታ ኢየሱስ ለኃጢአተኞች ያለውን ጥልቅ ፍቅር ማሳያ ነው። ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ ጌታ ያመጡት ምን አይነት አስተያየት ይሰጥ ይሆን ብለው ሊፈትኑት ነበር። የሙሴ ህግ ስታመነዝር የተገኘች ትወገር ይላል:: ጻፎችና ፈሪሳውያን በወቅቱ ከነበረው የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር ማንንም በቀላሉ መውገር አይችሉም። ምክንያቱም መላው የአይሁድ ሕዝብ በሮማውያን ቅኝ ግዛት ውስጥ ስለነበር ያለ ሮማውያን የፖለቲካ ፈቃድ አንድ አይሁድ ሌላውን አይሁድ የመግደል መብት አልነበረውም። ይህ ሁኔታ  የመውገር አቅማቸውን ሽባ አድርጎታል። ማንም አይሁዳዊ ያለ ሮማውያን ፈቃድና ነፃነት ሰው ገድሎ ከተገኘ ከፍተኛ ቅጣት ይጠብቀዋል።

➢ጻፎችና ፈሪሳውያን ጌታ ኢየሱስ ትወገር ካለ ሰው መውገር በሮማውያን ዘንድ ስለሚያስጠ ይቅ  መውገርን ያበረታታል ብለው ከፖለቲካ ጋር አገናኝተው የሮማውያንን ህግ ተላለፈ ብለው ሊያጠምዱት ነው።

እንዲሁም አትወገር ካለ ደግሞ ይህ ሰው የሙሴን ህግ ሊሽርና ኃጢአትን ሊያበረታታ ነው  የመጣው ብለው  አክራሪ አይሁዶችን ሊያስነስቡት ነው።

ስለዚህ የኛ ጌታ ቀጥተኛ መልስ ሳይሆን ተዘዋዋሪ መልስ መለሰላቸው። ትወገርም አትወገርም አላለም። ነገር ግን ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ ይውገራት አላቸው።ይህ የጠቢብ መልስ በትዕቢት እና በሀይማኖት ታውረው ህዝቡን ላሳወሩት ጻፎችና ፈሪሳውያን ያልተጠበቀ ዱብዳ የሆነ መልስ ነበር።

እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች። ዮሐ 8:9

ጌታ ኢየሱስ የዓለምን ኀጢአት ሊያስወግድ ውድ የሆነውን ደሙን ለሰው ልጅ ሁሉ  አፍስሷል።ክርስቶስ ያፀደቀውን  አክራሪ ኃይማኖተኞችም ሆኑ አጋንንት መክሰስ አይችሉም።

እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው?  ሮሜ 8:33

➢ክርስቶስ ፅድቃችን ነው።ክርስቶስ ፅድቃችን ነው ሲባል በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛነ ታችን እና ምሉዕነታችን ማለት ነው።ጌታ ኢየሱስ አሰማምሮ እና አቆነጃጅቶ ለእግዚአብሔር  አብ መልካም የመዓዛ ሽታዎች እንድንሆን ፅድቃችን ሆነ። ክርስቶስ ፅድቃችን ብቻ ሳይሆን የፅድቃችን ዋስትናም ጭምር ነው።
➢ጌታ ኢየሱስ ያፀደቀውን የትኛውም ኃይል ሊኮንነው አይችልም።ጌታ ኃጢአተኞችን ሊያፀድቅ ዝም ያሰኛቸው ብዙ ፈሪሳውያን አሉ።የሰው ጽድቅ የመርገም ጨርቅ ነው፤ የአማኞች ጽድቅ ግን ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።

➢ስለዚህ የአማኞች ድርሻ በጽድቅ ንቃተ ህሊና መመላለስ ነው። አማኝ ለመጽደቅ እንደሚኖር ሰው ሳይሆን እንደጸደቀ ሰው መኖር አለበት።

ክፍል 53 ይቀጥላል

መሳይ አለማየሁ(ነቢይ)

👇💐👇💐👇💐👇💐👇💐
            @KALTUBE
            @KALTUBE
            @KALTUBE
በክርስቶስ   IN CHRIST
ክፍል 51

         እንደ አንበሳ ያለፍርሃት መኖር

ኀጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለ ፍርሃት ይኖራል። መጽሐፈ ምሳሌ 28 : 1

➢አንዱ የፃድቅ ሰው(በክርስቶስ ኢየሱስ አምኖ የዳነ ሰው)መገለጫ እንደ አንበሳ ያለፍርሃት መኖሩ ነው። መፍራት የሌለብን የሚያስፈራራ ነገር ስለሌለ ሳይሆን የማንነት ለውጥ ስላደረግን ነው።

➢ ፍርሃት ዘርፈ ብዙ በሆነ የህይወት ጉዳዮች ውስጥ የሰውን ልጅ  አስሮ የሚይዝ የስሜት ተፅዕኖ ነው። ፍርሃት በተለያዩ መንገዶች ሊፈጠር ይችላል።ሁለት አይነት ፍርሃት አለ አንዱ ጤናማ የሆነ ፍርሃት ሲሆን ሁለተኛው ጤናማ ያልሆነ። ጠናማ ፍርሀት እግዚአብሔ ርን መፍራት ሲሆን ጤናማ ያልሆነው ፍርሃት ከስጋት፣ከጭንቀት፣ ከአጋንንት ተፅእኖ የሚመጣ ፍርሃት ነው።
➢ቃሉ ደጋግሞ አትፍሩ የሚለው የፍርሃት አይነት ሰዎችን ባርያ አድርጎ የሚገዛውን ፍርሃት ነው።

➢ፍርሃት የዲያብሎስ አንዱ የክፋት ስትራቴጂካዊ አሰራሩ ነው።ድፍረት ደግሞ የእግዚአብሔር አሰራር ነው። ይህ ድፍረት ቅዱስ ድፍረት ነው።እግዚአብሔር ሰዎችን ከፍርሃት ባርነትና ወጥመድ ሁለንተናቸውን ነጻ በማድረግ ይጠቀምባቸዋል እንጂ በፍርሃት ውስጥ ይኖሩ ዘንድ ፈቃዱ አይደለም። ቃሉ ማንንም እንዲሁም ምንም እንዳንፈራ ደጋግሞ ይመክረናል።

➢ ቆም በሉና ያስፈራችሁን የትኛውንም ነገር ወደ ጌታ አምጡት።ለመሆኑ ያስፈራችሁ ነገር ከእናንተ ጋር ካለው ከኢየሱስ ጋር ይወዳደራል? ያስፈራችሁ ነገር ለእግዚአብሔር የሚያስፈራው ይመስላችኋል? በፍርሃት ውስጥ ስትሆኑ እግዚአብሔር ዝም ብሎ የሚያያችሁ ይመስላችኋል?በፍጹም ! አንድ ነገር ማስተዋል ተገቢ ነው። ላስፈራችሁ ነገር የእግዚአብሔር ምላሽ ምን እንደሆነ ስትረዱ ፍርሃት ከእናንተ ህይወት ስፍራ እያጣና እየራቀ ይመጣል።

በፍርሀት ውስጥ እንኳን ብትሆኑ መንፈስ ቅዱስ ላስፈራችሁ ነገር የሚሰጠውን ምላሽ በቃሉ ውስጥና በውስጥ መንፈሳችሁ የሚናገራችሁን ቃል አዳምጡና ከራሳችሁ ጋር በእምነት አዋህዱት።

➢እናስተውል ፍርሃት እራሱ እግዚአብሔርን ይፈራል።ስለዚህ ያስፈራችሁን የትኛውንም ነገር በጌታ ፊት አቅርቡት፣እግዚአብሔርን ተማመኑ፣ አትፍሩ፤ለፍርሃት እጅ እንዳትሰጡ፣አይዟችሁ።

➢እናንተ የይሁዳው አንበሳ ልጆች ናችሁ።የአንበሳ ልጅ አንበሳ ነው። እናንተ ምናምንቴ አይደላችሁም።እናንተ ሰይጣን እንደሚላችሁ አይደላችሁም። እናንተ ሁኔታና ወጀቡ እንደሚለው አይደላችሁም። እናንተ ሰዎች እንደዛቱባችሁ አይሆንባችሁም።የፈራችሁት ነገር እናንተን አይወርሳችሁም።

➢እናንተ የሃይልን መንፈስ በክርስቶስ ኢየሱስ ተካፍላችኋል። ስለ ማንነታችሁ ባላችሁ  ዕውቀት ፅኑ።አንበሳ መቼም ቢሆን እንደ ፍየል ወይም እንደ ፈሪ እንሰሳ አይኖርም።አንበሣ ሁሌም አንበሣ ነው።አንበሳ ሲተኛም፣ ሲበላም፣ ሲጠጣም፣ ሲያድንም ሁሌም አንበሳ ነው።

➢ ፈሪ የምንሆንበት ምንም አይነት መንፈሳዊ ምክንያት የለም። ፍርሃት በእናንተ ህይወት ውስጥ የመንቀሳቀስ ህጋዊ መብት የለውም።
የእግዚአብሔር ቃል ውስጥ 365 ጊዜ ስላለመፍራት ተጠቅሷል።ስለዚህ እንደ አንበሳ ውጡ ግቡ። እናንተ አለም ላይ ምርጡ ዘር እና ከፍተኛ የሰማይ ጥበቃ የሚደረግላችሁ የሰማይ አምባሳደሮች ናችሁ። የሚጠብቃችሁ እግዚአብሔር አይተኛም አያንቀላፋም።እናንተ በአጠገባችሁ ሺህ በቀኛችሁ አስር ሺህ የሚወድቅላችሁ የእግዚአብሔር ህዝቦች ናችሁ።እናንተ በእግዚአብሔር አይን ውስጥ ናችሁ። ምንም አትፍሩ። በጌታ ተማምናችሁ ያለፍርሃት አገልግሉ፣ስራችሁን ስሩ፣ የጀመራች ሁት  ነገር ቀጥሉ። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነው።

እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። 2ጢሞ 1:7

መሳይ አለማየሁ (ነቢይ)

ክፍል 52 ይቀጥላል

👇💐👇💐👇💐👇💐👇💐
            @KALTUBE
            @KALTUBE
            @KALTUBE
🖥ክፍል ሁለት፣ በአምላክ ጥላ


🗣️“እግዚአብሔርን፦ አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ።”

            — መዝሙር 91፥2


አግዚአብሔር እምነትንና ጥበቃን አንድ ላይ አዋህዶ የያዘ ፈቃር አምላክ ነው። ለሰብአዊያን ታማኝ መሆኑን አምላክ ሰው በመሆን መስቀል ላይ ተቸንክሮ ሕያው ምስክር ሆነን። ጥበቃውን ደግሞ በመንፈሱ ሰውሮ ዘውትር አብሮነቱን ገለጠልን። “እግዚአብሔርን፦ አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ።” (መዝ 91፥2) የተባለው ቅኔ እነዚህን የአምላክ ባህሪያት አንፀባርቆልን እናገኛለን።


አንደኛ፣ አንተ መታመኛዬ ነህ

እምነታችንን በተለያዩ ነገሮች ላይ የማድረግ ልማድ ይኖረን ይሆናል። ገንዘብ፣ ስልጣን፣ ዝና፣ ሰው፣ ጥበብ ልብን የሚያዘነብሉ ነገሮች ናቸው።  በእርግጥ እነዚህ ነገሮች በራሳቸው ችግር የሚያመጡ ባይሆንም እምነት ሲጣልባቸው ግን የስህተት ጥግ ውስጥ ይከታሉ። ዓይንን ከአምላክ ላይ በማንሳት ወደ ጥፋት ጎዳና ይመሩናል።

እምነት ሊጣልበት የሚገባው እግዚአብሔር ብቻ ነው። እርሱ ቢታመኑት የሚታመን፣ ልብን ቢሰጡት በንፅህና የሚጠብቅ መልካም አምላክ ነው።


ሁለተኛ፣ አንተ መሸሸጊያዬ ነው

አምላካችን እምነት የሚጣልበት ብቻ ሳይሆን የሚሸሸጉበትም ጭምር ነው። በመከራ ሰዓት በእቅፉ ውስጥ ሸሽጎ ያስመልጠናል። ከውጪ ያለው የሕይወት ማዕበል እርሱ ጋር ሲደርስ አቅምን ያጣል። ወገኖቼ፣ መሸሸጊያችንን በእግዚአብሔር እስካደረግን ድረስ እርሱን አልፎ ሊያጠቃን የሚችል አንዳች ነገር አይኖርም። ይህ ትልቅ መበርቻ ነው።


🖥ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ መታመኛዬና መሸሸጊያዬ ስለሆንክ አከብርሃለሁ። የልቤ ማረፊያ ዘውትር አንተ ጋር ይሆን ዘንድ በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።
በክርስቶስ IN CHRIST

ክፍል 50

        የመዝራትና የማጨድ መርህ

ይህንም እላለሁ፦ “በጥቂት የሚዘራ፡ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፥ በበረከትም የሚዘራ፡ በበረከት ደግሞ ያጭዳል።”እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም። 1ቆሮ 9:6-7

👉መዝራትና ማጨድ ተፈጥሯዊም መንፈሳዊም መርህ ነው።
አንድ ገበሬ በእጁ ላይ የያዘውን ዘር አስፈጭቶ የሚበላ ከሆነ ለቀጣይ ጊዜ የሚተርፈው ነገር ስለማይኖር መሬቱ ፆሙን ያድራል። ቀጥሎ በምግብ እጦትና በረሀብ ይጠቃል።

➢ብልህ ገበሬ ግን ዘሩን ለሆዱ ሳይሆን  ለቀጣይ ፍሬያማነትና ምርታማነት ይሆን ዘንድ  በእርሻው ላይ ይዘራዋል።የዘራውም ዘር ብዙ ፍሬ አፍርቶ ከራሱ አልፎ ለሌሎች በረከት ይሆናል።

➢መዝራትና ማጨድ የእግዚአብሔር  የፋይናንስ ፖሊሲ ነው።በዚህ ፖሊሲ መሰረት
መስጠት መቀበል ነው፤ መዝራት ማጨድ ነው።

➢መስጠት ሲባል በገንዘባችን ለእግዚአብሔ ር ምን ያክል እንደምንገዛ ማሳያ መንገድ ነው። መስጠት ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር የምንገልፅበትና ለእሱ እንደምንገዛ ማሳያ ነው።
➢መስጠት  በህይወታችን ያገኘነውን ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር እንደተቀበልነው መመሰከርያ መንገድ ነው።  በመሰረቱ ለእግዚአብሔር ልንሰጠው የምንችለው አንዳች ነገር የለም።ለእግዚአብ ሔር ምን ይሰጠዋል?? ስጦታዎቻችችን  ተገብቶትና በቅቶት ነው የምንሰጠው ወይስ ፍቅራችንን ለመግለጽ ብለን ነው?

➢መዝራትና ማጨድ በመስጠት ውሰጥ ያለውን በረከት ማጣጣሚያ መንገድ ነው።
ሰጪነት የእግዚአብሔር ባህሪ ነው። እግዚአብሔር እጅግ ለጋስ አምላክ ነው።

➢መስጠት ብዙ የፋይናንስ ቀውሶችን ያስወግዳል።በመስጠት ብቻ የሚሰባበሩ የፋይናንስና የበረከት ገደቦች አሉ።
መስጠት መባረክንና በረከትን በህይወታችን እውን ያደርጋል።
➢ስንሰጥ የልብ መነሻችን(ሞቲቭ) ደስታ ሊሆን ይገባል ይላል ቃሉ። ስንሰጥ በኀዘን ሊሆን አይገባም። ምክንያቱም እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ሲሰጠን ደስ ብሎት ነው የሰጠንና።

ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣች ኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁ ንም ፍሬ ያሳድጋል፤  1ቆሮ 9:10

➢በመስጠት ህይወት ውስጥ በቀጣይነት  ሰጪነታችንን እናረጋግጣለን።ስንሰጥ የምንሰጠውን አብዝቶ የሚሰጥ ጌታ አለ።
  
             ለምን ዓላማ ልስጥ??

1ኛ ለወንጌል ዓላማ (ለቤተክርስቲያን አገልግሎት)

ከእግዚአብሔር መንግስት ጋር ሽርክና የገባ ማንኛውም ሰው ትርፋማ እና  ለትውልድ ሁሉ በረከት መሆን ይጀምራል።የእግዚአብሔር መንግስት ኢኮኖሚ የማይናጋ እና የተደላደለ ነው።ስለዚህ በዚህ መንግስት ላይ ዘርታችሁ ኪሳራ የሚባል ነገር አይታሰብም።

2ኛ ድሆችን መርዳት

ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፥በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል።
        ምሳሌ 19:17

     ብዙ ብር ስለሌለኝ መስጠት የለብኝም?

መስጠት ከልብ ሃሳብ ጋር የተቆራኘ ነው።ጌታ ከምንሰጠው  ስጦታ በላይ ልባችንን ያያል። ለመስጠት ትልቅ ልብ ካላችሁ ስጦታችሁ ትልቅ ነው። በጥቂቱ መስጠት ጀምሩ፣ካላችሁ መስጠት ጀምሩ ያኔ የሌላችሁ ሁሉ ይጨመርላችኋል። እግዚአብሔር አብዝታችሁ ትዘሩ ዘንድ ዘርን ይሰጣችኋል።

መሳይ አለማየሁ (ነቢይ)

ክፍል 51 ይቀጥላል

👇💐👇💐👇💐👇💐👇💐
            @KALTUBE
            @KALTUBE
            @KALTUBE
🖥ክፍል አንድ፣ በአምላክ ጥላ


🗣️“በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል።”

            — መዝሙር 91፥1


መዝሙር ዘጠና አንድ የእግዚአብሔርን ጥበቃ በደማቅ ቀለማት አስፍሮልን እናገኛለን። ይህ ዝማሬ ከእርሱ የሆነው ጥበቃ ሁሉ አቀፍ መሆኑን ይጠቅሳል። በሚቀጥሉት አምስት ተከታታይ ቀናት "በአምላክ ጥላ" በሚል ርዕስ ከዚህ ክፍል ትምሕርትን እንቀስማለን።


ይህ የመዝሙር ቅኔ “በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል።” (መዝ 91፥1) በሚሉ ግሩም ቃላቶች ጅማሬውን ያደርጋል። ልጆቹን በማትረፍረፍና ለልጆቹ በመትረፍ የሚታወቀው አምላክ በዚህ ክፍል ላይ መጠጊያ ሆኖ ቀርቧል።


አንደኛ፣ የሚኖር

እግዚአብሔር የቅርብ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለም። እርሱ ከእስትንፋሳችን ይልቅ ለእኛ የቀረበ ቅርባችን ነው። የቀረበን ጌታችን ደግሞ መኖሪያችንም ጭምር ነው። ሕያው አምላክ ጉዳችንን በምሕረቱ ሽሮና በደላችንን በይቅርታ ትቶ ከእርሱ ጋር የመኖርን የከበረ ዕድል ሰጠን።


“በልዑል መጠጊያ መኖር” መባረክ ነው። ምድርንና የዓለምን ብልጭልጭታ ወዲያ ብሎ ጥሎ አምላክ ፊት መቅረብ ፍፁም እርካታን ይሰጣል። ጠላት “በልዑል መጠጊያ” እንዳንኖር የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም። ይህ ክፉ ከእርሱ ጋር በጨለማ ሰንሰለት ታስረን ዘመናችንን እንጨርስ ዘንድ መሻቱ ነው። ከመኖር በፊት የነበረ፣ በፀጋው የሚያኖር እግዚአብሔር ብቻ ነውና “በልዑል መጠጊያ” ለመኖር ልባችንን እናዘንብል።


ሁለተኛ፣ ጥላ

መጠጊያውን አምላኩ ጋር ያደረገ ሰው ማደሪያውን በእርሱ ጥላ ውስጥ ያደርጋል። እግዚአብሔር ከሀሩሩ ወላፈን፣ ከውሽንፍሩ ማዕበል ተከልለን የምናመልጥበት ጥላችን ነው። በዚህ በአምላክ ጥላ ውስጥ እስካለን ድረስ ፍፁም ተጠብቀን እንኖራለን።


📣ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ “በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል።” ተብሎ በቃልህ እንደ ተፃፈ መኖሪያዬንና ማደሪያዬን ከአንተ ጋር አድርግልኝ። አሜን።

💬 የህይወት ስንቅ ~ #BT
 🔗🔗@KALTUBE
በክርስቶስ     IN CHRIST
ክፍል 49

መንፈሳዊ  ድምፆችን መለየት

አንድ ክርስቲያን በመንፈስ አለም የተለያዩ ድምፆች መኖራቸውን መረዳት ሲጀምር ድምፆችን መለየት ይጀምራል።

      ሶስት አይነት ድምፆች

1ኛ የእግዚአብሔር ድምፅ
ከክፍል አንድ ጀምሮ ስናይ እንደቆየነው  የእግዚአብሔር ድምፅ የሰላም፣የፀጥታና የደስታ መርበብ ነው።

የእግዚአብሔር ድምፅ ዳግም የተወለዱ ክርስትያኖች  የሚረዱት የመንፈስ ድምፅ ነው።መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዱ አማኝ ህይወት ውስጥ ስላደረ ለልብ ይናገራል።
የጌታ ቃል ''በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ '' ስለሚል
ይህ ድምፅ ወደ አማኞች የሚመጣ የሰማይ ድምፅ ነው።

2ኛ የሰይጣን ድምፅ
የሰይጣን ድምፅ አታላይ ድምፅ ነው።
እባቡ ወደ ሄዋን መጥቶ በተንኮል እንዳሳት ሁሉ ይህ ድመፅ ሰዎችን ሁሉ እያሳመነ የሚያስት ድምፅ ነው። ይህ ድምፅ የተስፋ መቁረጥ፣ የጭንቀት፣ የግራ መጋባት ድምፅ ነው።

ሰይጣን የብርሀን መልአክ መስሎ ለማታለል የማያደርገው ጥረት የለም። አንዱ ማታለያ መንገዱም የራሱን ድምፅ እንደ እግዚአብሔር ድመፅ አስመስሎ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ለማግኘት መሞከር ነው።የሰው ልጅ የሰይጣንን ድምፅ የእግዚአብሔር ድምፅ መስሎት የሰማ ቀን ህይወቱ መጨለም ትጀምራለች።

ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና።እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።      2ቆሮ11:13-14

የሰይጣን ድምፅ ዋና ዋና ማስተላለፊያ መንገዶች

ሀ) የሐሰት ትምህርት
(የሐሰት ትምህርት ዋነኛው የሰይጣን ድምፅ ነው)
አማኞች ከእውነተኛው የክርስቶስ ትምህርትና መረዳት ወጥተው ለጆሮ ወደሚመች፣ለስጋዊ ነገሮች ማሟያ ወደሆኑ የተለያዩ ትምህርቶች ዘወር እንዲሉ ያደርጋል።

ለ) የጨለማ ህልሞች :-
ሰይጣን ብዙዎችን ለማሳት የሚሞክረው በህልም በኩል ነው። በህልም ብዙዎችን ከህልማቸው ለማስቀረት ይጥራል። ብዙዎች በህልማቸው አልባሌ ህልሞችን ፣የዝሙት ህልሞች፣ የሞት ህልሞች፣ የውድቀት ህልሞች ደጋግመው ያያሉ።የዚህ ህልም አላማ ሰዎች በህልም ያዩትን በእውን እንዲፈፀምባቸው ነው።ስለዚህ እያንዳንዱ አማኝ ወደ መኝታው ከመሄዱ በፊት እለት እለት መፀለይ አለበት።እንዲሁም የሐጢአት ልምምዶች ውስጥ ካለ ቶሎ ብሎ ከራሱ ላይ መቁረጥ አለበት።

ሐ)አጋንንታዊ ምክሮች
(ሰይጣን በተለይ በሚያሰቱ ምክሮች ብዙዎችን እየመከረ ወደ ድቅድቅ ጨለማ ጨምሯል) የሰይጣን ምክር የሚያንፅ ሳይሆን የሚያፈርስ የተቀነባበረ ሴራ ነው። ይህ ሴራውን የሚሰራው ምናልባት ቀላል በሚመስል የህይወት ጉዳዮቻችን ላይ ነው። ሰይጣን ብዙዎችን ስለገንዘብ፣ስለ ትዳር፣ስለ ስኬት፣ስለ ትምህርት ፣ስለ ስልጣን፣ስለ በላይነት ወዘተ ባላቸው መረዳት የተንሻፈፈ መረዳት እንዲኖራቸው ያሳምናቸዋል።

መ) የሐሰት ትንቢቶች : 
ሰይጣን ከየትኛውም ዘመን በላይ የውሸት ትንቢት (Fake prophecy) እንደ ትልቅ መሳርያ እየተጠቀመበት ይገኛል።
ለዛም ነው የእግዚአብሔር ቃል ትንቢትን ሳንንቅ እንድንመረምር የሚመክረን።

ስለዚህ ትንቢቶችን ስንሰማ በጥሞና በማዳመጥ በመንፈስና በቃል መመርመር አለብን።

  3ኛ የስጋ ድምፅ
የስጋ ድምፅ ሲባል ከኃጢአተኛው ተፈጥሮ የሚመነጭ የስጋ ድምፅ ነው። ይህ ድምፅ ሁሌ የሚጮኸው ስለ ስጋ ጉዳዮች በማስተጋባት ነው።

ዋናው የስጋ ድምፅ አላማ የህይወታችን ማዕከል መንፈሳዊነት ሳይሆን ስጋዊነት እንዲሆን ነው።

የስጋን ድምፅ ከሰማን ህይወት ስጋ ስጋ ትላለች። ሰው ያለ ክርስቶስ ጠረንና መአዛ ሙት ነው። ስለዚህ የስጋ ድምፅ የመጨረሻው ግብ ከክርስቶስ ኢየሱስ ህይወት ሰውን ማጉደል ነው።

የስጋ ድምፅ  በአዕምሯችን ላይ ደጋግሞ የስጋ ነገሮች ገነው እንዲታዩ ይጮሀል። በዚህ ጊዜ የስጋን ድምፅ ንቀንና ክደን እራሳችንን ለክርስቶስ ፀጋ ልናስገዛ ይገባል።

ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።  ዕብ 4:12-13

መሳይ አለማየሁ(ነቢይ)

    ክፍል  50   ይቀጥላል

👇💐👇💐👇💐👇💐👇💐
            @KALTUBE
            @KALTUBE
            @KALTUBE
በክርስቶስ IN CHRIST
ክፍል 48

መልካሙን ባህሪ መገንባት

ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ።
ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥
ገንዘብን የሚወዱ፥
ትምክህተኞች፥
ትዕቢተኞች፥
ተሳዳቢዎች፥
ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥
የማያመሰግኑ፥
ቅድስና የሌላቸው፥
ፍቅር የሌላቸው፥
ዕርቅን የማይሰሙ፥
ሐሜተኞች፥
ራሳቸውን የማይገዙ፥
ጨካኞች፥
መልካም የሆነውን የማይወዱ፥
ከዳተኞች፥
ችኩሎች፥
በትዕቢት የተነፉ፥
ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤
የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። 
1ጢሞ 3:1-5


➢የሰው ክፉ ባህሪ ለሰይጣን እንደ ፈረስ ነው። ሰይጣን የሰውን ክፉ ባህሪ ይጋልባል።ሰይጣን መንፈስ ነው፤ የሰው ክፉ ባህሪ ውስጥ ሲገባ ግን ተጨባጭ መሆን ይጀምራል። ሰይጣን ክፋቱ በሙላት የሚገለጠው በሰዎች ባህሪ በኩል ነው። ሰይጣን ክፉ መሆኑን ያወቅነው ክፉ ሰዎችን አይተን ነው። ለምሳሌ ፈረኦን፣ ናቡከደነፆር፣ሄሮድስ የመሳሰሉ ጨካኝ ነገስታት መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስናነብ አጋንንታዊ ባህሪ ያላቸው ሰዎች እንደሆኑ በቀላሉ እንረዳለን።

➢ ከላይ በመግቢያ ጥቅሳችን ላይ ያነበብነው 19 ክፉ ባህርያት በመጨረሻው ዘመን በሰዎች ባህሪ የሚገለጡ አጋንንታዊ ባህርያት ናቸው።

➢ ክፉ ባህሪ እንዲያው በአንድ ቀን የሚበቅል አይደለም።ባህሪ ባህሪ ከመሆኑ በፊት የሚቀድሙ ነገሮች አሉ።እነሱም እውቀት፣ አስተሳሰብና ልማድ ናቸው።ሦስቱ ከእኛ ጋር ሲዋሀዱ ባህሪያችንን ወይ በአሉታዊ መልኩ አሊያም በአዎንታዊ መልኩ የመቅረፅ ኃይል አላቸው።ሳናቀው በአዕምሯችን ውስጥ የተጠራቀሙ አላስፈላጊና የተንሻፈፉ እውቀቶች ባህሪን በአሉታዊ መልኩ ይቀርፁታል።

➢ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፈሶን ቤተክርስቲያን መጋቢ ለጢሞቴዎስ የፃፈው መልእክት ልብ ላለው ጠቢብ አማኝ ወሳኝ ምክር ነው።

➢በዚህ በዘመን መጨረሻ ላይ እየኖርን ያለን አማኞች ማወቅ ያለብን ሰይጣን ምን ያክል የሰዎችን ባህሪ ተጠቅሞ ከሰውነት ተርታ ዝቅ እንደሚያደርግ እና እንዴት አድርጎ መንፈሳዊ ውጊያ እንደሚያካሄድ ነው። ይህ አይነቱ አጋንንታዊ የውጊያ ዘዴ በግሳፄ ሳይሆን በአዕምሮ መታደስ የሚለቅ ነው።

➢ በዚህ ዘመን የምናየው አብዛኛው ቀውስ የባህሪ ቀውስ ነው።ሰይጣን የአንድን ሰው መላ ህይወት ማቃወስ ከፈለገ ባህሪውን ብቻ ነው የሚያቃውሰው። ከዛ ሰዎች የክፉ ባህርያቸው እስረኛ ሆነው ለረጅም ዘመን ይቆያሉ። ለዚህ ነው የእግዚአብሔር ቃል ደጋግሞ በአዕምሮ ስለመታደስ የሚናገረው።
አዕምሯችን በቃሉ ካልተገራ ባህርያችን ከቃሉ ቁጥጥር ውጪ ይሆናል።በአዕምሮ መታደስ ቅፅበታዊ ሳይሆን ሂደታዊ ነው። 

➢ የሰው ባህሪ ከተቃወሰ የማይቃወስ ነገር የለም።የግል ህይወት ይቃወሳል፣ ቤተሰብ ይቃወሳል፣ ማህበራዊ መስተጋብር ይቃወሳል፣ መንፈሳዊ ህይወት ጥያቄ ውስጥ ይገባል።
➢ እኛ የሰው ልጆች ከባህሪያችን ማምለጥ አንችልም።ባህርያችን እኛነታችን ነው።

➢ባህርያችን ጤናማ እንዲሆን አስተሳሰባችን ጤናማ ሊሆን ይገባል። ስለዚህ አዕምሯችንን
ምን እየመገብነው ነው?? አለማዊነትን ወይስ መንፈሳዊነትን?

ክፍል 49

መሳይ አለማየሁ(ነቢይ)

👇💐👇💐👇💐👇💐👇💐
            @KALTUBE
            @KALTUBE
            @KALTUBE
🖥ዝም ታሰኘዋለህ


🗣️“የባሕርን ኃይል አንተ ትገዛለህ፥ የሞገዱንም መናወጥ አንተ ዝም ታሰኘዋለህ።”

           — መዝሙር 89፥9


ዝማሬን ማድመጥ ሀሴትን ይሰጠኛል። ልቤንና ሀሳቤን አንድ ላይ አዋህጄ የፈጠረኝን አምላክ በአንደበቶቼ ሳመሰግን ነፍስም አይቀርልኝ። የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ሕያው ቃላቶች ከዜማው ጋር ተዋዝተው ግሩም የሆነን ዝማሬ እንድናደምጥ እድሉን ይሰጡናል። ታዲያ ሁሉም ዝማሬ ተመሳሳይ ቅኝት የለውም። የተለያዩ የዜማ ስርዓቶችና ቅኞቶች አንድ ላይ በመተባበር ዘውትር ቢሰሙ የማይሰለቹና ጣፋጭ የሆኑ ዝማሬዎችን ይሰጡናል።


ሕይወትም ልክ እንደ ዝማሬ የብዙ ነገሮች ድብልቅ ውጤት ነው። ሁሉም ዝማሬ ተመሳሳይ ቅኝት እንደማይኖረው ሁሉ፣ ሕይወትም ልክ እንደዚሁ ነው። የምስጋና ቅኝት፣ የደስታ ቅኝት፣ የምሬት ቅኝት፣ የሀዘን ቅኝት በሕይወት ውስጥ በጉልህ ተንፀባርቀው ይገኛሉ። ይህ ሕይወት የብዙ ህብረ ቀለማት ውጤት እንደ ሆነ ይነግረናል።


ነገር ሁሉ ሰምሮልን ቤታችን በስኬት ሲጎበኝ፣ ሕይወታችን የሀሴትን ቅኝት ተቀኝቶ ደስታን ይሰጠናል። ነገር ግን ሁሌም ነገሮች እንደዚህ ላይቀጥሉ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ የሀሴት ቅኝታችን ስፍራውን ለለቅሶ ቅኝት ይለቃል። በዚህን ጊዜ ልብ ይደማል፣ ውስጥም ያዝናል። ላፍታ እንኳን አስበን በማናውቅበት ሁኔታ ቤታችን በታላቅ ማዕበል ይመታል። የማዕበሉ ማየል ለዘመናት የገነባነውን ሁሉ ይንዳል። ከባድ ሀዘን፣ ጥልቅ ህመም።


ዛሬ በእንደዚህ አይነት ከባድ የሕይወት ቅኝት ውስጥ እያለፍን ላለን ሰዎች በኤታን በኩል የተነገረውን ቃል ለልባችን እንንገረው፦ “የባሕርን ኃይል አንተ ትገዛለህ፥ የሞገዱንም መናወጥ አንተ ዝም ታሰኘዋለህ።” (መዝ 89፥9) ሀሌሉያ! ቤታችንንና ሕይወታችንን ሊበትን የመጣው ማዕበል በእግዚአብሔር ዝም ይላል። የተናወጠው ሞገድ አቅሙን ያጣና ፀጥ ረጭ ይላል። ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን! ስለዚህ የማዕበሉ ማየል ልባችንን አያርደርው። የሕይወት ቅኝታችን መለወጡ አያሸብረን። ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ የበላይ የሆነ አምላክ እነሆ በሰማይ አለና።


🖥ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ “የባሕርን ኃይል አንተ ትገዛለህ፥ የሞገዱንም መናወጥ አንተ ዝም ታሰኘዋለህ”ና አከብርሃለሁ። ሕይወቴ ደግሞ በመከራ ቅኝቶች ሲያልፍና ክራሬ ለጆሮ ሰቅጣጭ የሆኑ ድምፆችን ሲያወጣ አንተ ማዕበሌን ዝም እንደምታሰኝ በማመን ወደ ፀጋህ ዙፋን በእምነት አስጠጋኝ። አሜን።

🗣️ የህይወት ስንቅ ~ #BT
 🔗🔗@KALTUBE
📢 In a world full of noise, hear what truly matters. 🎧
👂 Listen to the Word of Faith, wherever you are!
With over 7,500 worship songs and 650+ albums, Humble Melody brings the power of worship songs to your fingertips – anytime, anywhere. 🌍🎶
🔹 Telegram: 📲https://t.me/humble_melody
🔹Facebook: 👍https://web.facebook.com/profile.php?id=61554748534187
🔹Instagram: 📸https://www.instagram.com/humblemelody_/?hl=en
በክርስቶስ IN CHRIST
ክፍል 47

           መክሊትህን አትቅበረው

መክሊታችንን ለእግዚአብሔር ክብርና ለወንጌ ል አላማ ማዋል በሰማይም በምድር ም ታላቅ ሽልማት አለው።የተሰጠንን መክሊት በማትረፍ ንቁ እና ጥበበ ኛ ልንሆን ይገባል፣ መክሊቶቻችንን ፈልገን በማግኘት በመክሊታች ን ለማይጠፋው ህይወት ልንተጋ ይገባል።

መክሊትህ ምንድ ነው?
ቃሉ እንዲህ ይላል.....

''ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናል ና፤  ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤  እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ።  አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘ ብ ቀበረ።
ማቴ 25:15

ሰዎች ለምን ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን መክሊት ይቀብራሉ?


1,በእጃቸው ላይ ያለው መክሊት አደራ እንደሆነ ስለማያውቁ ሊሆን ይችላል
2,ስንት መክሊት እንደተቀበሉ እውቀት ስለሌላቸው ሊሆን ይችላል፣
3,መክሊታቸውን እንዴት ማትረፍ እንዳለባቸው ስለማያውቁ ሊሆን ይችላል፣
4,አመጸኞች ስለሆኑ ሊሆን ይችላል፣
5,ለተቀበሉት መክሊት ትኩረት ባለማድረጋቸው
6,መክሊትን ማትረፍ ከእግዚአብሔር ሽልማት እንዳለው ባለማወቃቸው፣
7,የተሰጣቸውን መክሊት ትተው በሌላው ሰው መክሊት የመጠመድ አባዜ ስላለባቸው ሊሆን ይችላል፣
8,መክሊታችንን ከሌላው ሰው መክሊት ጋር ማወዳደር መጀመር።
9,ስለ መክሊት ያላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ
10,ዋጋቢስ በሆኑ ነገሮች መጠመድ፣
11,ሰዎች መንፈሳዊ እውነታዎችን የሚረዱበት የውስጥ አይኖቻቸው ሳይከፈቱ ሲቀሩ መክሊታቸውን አውቀውም ሳያቁም ሊቀብሩት ይችላሉ።

➢መክሊትን ማትረፍ ከእግዚአብሔር የተቀበልናቸውን ነገሮች በሙሉ በትጋትና በኃላፊነት ስሜት ለእግዚአብሔር ክብር ማዋልና ለታላቁ ተልእኮ  መፈጸም መስራት ነው፤በመክሊትን ማትረፍ ማለት የተቀበልነውን ሁሉ ለማይጠፋው ህይወት መስራት ማለት ነው።

መሳይ አለማየሁ (ነቢይ)

ክፍል 48 ይቀጥላል

👇💐👇💐👇💐👇💐👇💐
            @KALTUBE
            @KALTUBE
            @KALTUBE
See more posts
TeleSearch